ስኬታማ አመራሮች አምስት የዉጤት ሚስጥራዊ ባህሪያት

ስኬታማ አመራሮች አምስት የዉጤት ሚስጥራዊ ባህሪያት

የስኬታማ አመራሮች አምስት የዉጤት ሚስጥራዊ ባህሪያት
===============================
ለአንድ ተቋም የላቀ ውጤታማነት ትልቁን ሚና የሚይዘው አመራሩ ነው፡፡
የአመራሩ ጥንካሬ ወይም ድክመት አንድን ትንሽ ተቋም አይደለም አገርን
ያህል ነገር ደካማ ወይም ጠንካራ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በተለያዩ ተቋማት
ውስጥ ያሉ አመራሮች የሚመሩት ድርጅት አትራፊም ይሁን ትርፋማ
ያልሆነ እስከ 40 በመቶ ድረስ ውጤታማነቱን የመወሰን አቅም አላቸው፡፡
አመራሩ የበታች ሰራተኞችን ይቀጥራል፣ ያሰራል፡፡ ድርጅቱ ውጤታማ
ባይሆን ተጠያቂው የሚሆነው ስራውን በበላይነት የሚያሰራው ወይም
ደግሞ ስራውን የሚሰሩ ሰዎችን የቀጠረው ነው ሊሆን የሚችለው፡፡
ለዚያም ነው አንድ ድርጅት ሲመሰረት አመራሩ ማነው ተብሎ በቅድሚያ
መለየት ያለበት፡፡
የምንመራው ተቋም የፖለቲካ ፓርቲ ሊሆን ይችላል፣ የእግር ኳስ ክለብ
ሊሆን ይችላል፣ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅትም እንዲሁ፡፡ በተመሳሳይ
መልኩ አትራፊ የንግድ ድርጅትም ሊሆን ይችላል፡፡ ሁሉም እንደ ተቋም
ግን የተቋቋመበትና ሊያሳኩት የሚፈልጉት ራዕይና ግብ አላቸው፡፡ ተቋምን
ተቋም ከሚያሰኙት አንዱ መለያ ባህሪያቸው ሰርቶ ሊያሳካቸው
የሚፈልጋቸው ግልፅ አላማዎች መኖራቸው ነው፡፡ እነዚህን ዳር
ለማድረስ ነው እንግዲህ የአመራሩ ሚና፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የምርጥ አመራር ባህሪያት ምንድን ናቸው?
አንድ አመራር ብቃት የ‹‹BASKET›› ፅንሰ ሃሳብን ያሟላ መሆን
አለበት፡፡ ሁሉም ሰው መሪ መሆን ቢፈልግም መሪ መሆን የሚችሉት ግን
ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ መሪ መሆን ችለውም የላቀ ውጤት ማስመዝገብ
የሚችሉት አሁንም ጥቂቶች ናቸው፡፡ የእጅግ ውጤታማ ሰዎች
አመራሮች አንድ መገለጫዎች ‹‹BASKET›› የተባለውን መስፈርት
የሚያሟሉ መሆናቸው ነው፡፡ ‹‹ባስኬት›› ሲባል ቅርጫት ለማለት ተፈልጎ
አይደለም፡፡ ምህፃረ ቃል ነው፡፡
#1. B- Behavior…ባህሪ!
“Leadership is a potent combination of strategy and
behavior. But if you must be without one, be without
strategy”… Norman Skhwarzkopf
እንደሚታወቀው አንድ አመራር ስለሚጠበቅበት የስራ ኃላፊነት ሊወጣው
የሚያስችለው ባህሪ ሊኖረው ይገባል፡፡ አንዳንዱ መሪ እንኳን ለመምራት
ለመመራት የማይሆን ባህሪ ያለው አለ፡፡ እንኳን ሌሎችን ሊመራ ራሱ
መሪ የሚያስፈልገው ሰውም አለ፡፡ የመሪነት ባህሪ ራሱን የቻለ ልዩ ገጽታ
ነው፡፡ ለዚያም ነው ሁሉም ሰው መሪ መሆን የማይችለው፡፡ ለዚያ
ኃላፊነት ዝግጁ የሆነ ባህሪ ሊኖረው ይገባል፡፡ አንድ ሰው በአገራችን
ካለው የሊደርሽፕ ተቋምም ሆነ ሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ቢማር
የመሪነት ባህሪ ካልታደለው ወይም ደግሞ በውስጡ ካላዳበረው
ውጤታማ መሪ ሊሆን አይችልም፡፡
መኪና ከፈለግንበት ቦታ ሊያደርሰን የሚችለው ጎማ ሲገጠምለት ነው፡፡
አንድ መሪም እንዲሁ የሚመራውን ተቋም ከዳር ማድረስ የሚችለው
ለአመራርነት የሚያበቃ ባህሪ ሲገጠምለት ነው፡፡ ከየትኛውም ተቋም
ውጤት በስተጀርባ የአመራሮችን ባህሪ እናገኛለን፡፡ ጥሩ ውጤት ያላቸው
ከሆነ ጥሩ የአመራር ባህሪ አላቸው ማለት ሲሆን ውጡቱ ደግሞ
ከተጠበቀው በታች ከሆነም ባህሪያቸው የዚያኑ ያህል ሆኗል ማለት
ይቻላል፡፡
አንድ የእግርኳስ አሰልጣኝ ለአሰልጣኝነት የሚሆን ባህሪ ከሌለው ቡድኑ
ውጤት ሊያመጣ አይችልም፡፡ አንድ የፖለቲካ ተቋም /ፓርቲ/ መሪ
ፖለቲካዊ መድረክን ወደ ውጤት ለመቀየር የሚያስችል አፈፃፀም
ከሌለው በተመሳሳይ መልኩ ፓርቲው እንኳን ምርጫ ተወዳድሮ ሊያሸንፍ
አይደለም የራሱን ህልውና ለማስጠበቅ እንኳን ሊሳነው ይችላል፡፡ አንድ
የንግድ ተቋም አመራር ለንግድ አመራርነት የሚያበቃ ባህሪ ከሌለው
ድርጅቱ አትራፊ ሆኖ ሊዘልቅ አይችልም፡፡ ይህ የሚያሳየን የአመራር
ባህሪ እንደየተቋሙ ባህሪ የሚለያይ መሆኑ ነው፡፡
ለዚያም ነው ታክሲ ሲነዳ የነበረ ሹፌር አውቶብሱን መንዳት የሚሳነው፡፡
አውቶብሱን ለመንዳት የሚያስችል ባህሪ ከዳበረ ግን በጥሩ ሁኔታ
መንዳት ይችላል፡፡ አንድ ቦ ለውጤት ያበቃ ባህሪ ለሌላም ሊያበቃ
የሚችል ሲሆን አንድ ቦታ ላይ ተፈትሾ ያልሰራ ባህሪ ደግሞ በሌላ ቦታ
ላይም ሊራ አይችልም፡፡ ሆኖም ለብዙ ተቋማት ውድቀት ትልቁ ምክንያት
ያ ተቋም የሚፈልገውን ልዩ የአመራር ባህሪ ካለመኖር ወይም ደግሞ
ካለማዳበር የሚመነጭ ነው የሚሆነው፡፡ ለዚያም ነው አንዳንዴ
በአመራር ብቃታቸው ሌላ ቦታ ውጤታማ ሆነው በሌላ ድርጅት ላይ
ሲቀጠሩ ድርጅቱን ሊጥሉት የሚችሉት፡፡ ይህም ማለት ባህሪ በየጊዜው
የሚዳብር፣ እንደምንመራው ተቋም ባህሪም በአዲስ መልክ የሚሻሻልና
ውጤትን የሚወስን አንዱ የመሪዎች ወሳኝ ገፅታ መሆኑን ነው፡፡
#2. A Attitude… አመለካከት
“If your actions inspire others to dream more, learn
more, do more and become more, you are a leader”
John Quincy Adams
ይህ የመሪዎች ሌላኛው ውጤት ቀያሪ መገለጫቸው ነው፡፡ የመሪዎች
ገንቢ አመለካት ለገንቢ ውጤት የሚያበቃ ኃይል አለው፡፡ አንድ መሪ
የድርጅቱን ራዕይ የራሱ ራዕይ አድርጎ ከመነሳት ይጀምራል፡፡ አንዳንድ
አመራሮች በአንድ ተቋም ላይ ለመሪነት ሲመረጡ ወይም ደግሞ ሲሾሙ
የድርጅቱን ራዕይ ላያውቁት ወይም ደግሞ ላያምኑበት ከቻሉ ግለሰቡና
ተቋሙ አልተዋወቁምና ከዚህ መሰል አመራር ውጤት መጠበቅ ማለት
ከጠራ ሰማይ ላይ ዝናም ይጥላል ብሎ ጥላ እንደመያዝ ነው
የሚቆጠረው፡፡ እንዲሁም የትኛውም የንግድ ተቋም ስራውን
የሚገዳደሩት ተወዳዳሪ ተቋማት አሉ፡፡ የንግድ ድርጅትን ብንወስድ
ከእነሱ ካልተሻለ ሊጥሉት የሚችሉ ተወዳዳሪዎ አሉት፡፡ በንግድ ውስጥ
ያለው አማራጭ፣ ወይም መምራት አልያም መውጣት ነው፡፡ ከፊት
መሪዎች ውስጥ አንዱ መሆን መቻል አለበት፡፡ የእግርኳስ ክለብንም
ብንወስድ እንዲሁ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲም ተፎካካሪዎች አሉት፡፡
በመሆኑም የትኛውም ተቋም በአሸናፊነት መንፈስ የተገነባ አመራር
ያስፈልገዋል፡፡ ተቋሙ ከሌሎች ተሽሎ የሚገኝ ተቋም እንደሆነና እሱም
ያንን በተግባር እውን ማድረግ እንደሚችል የሚያምን፣ ቁርጠኝነቱ
ያለው፣ አመራር ያስፈልጋል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ራሱንና ተቋሙን አሳንሶ
የሚመለከት አመራር እኩል ውጤት ሊያመጣ አይችልም፡፡
እንዲሁም የድርጅቱ ውጤት የእኔ ውጤት ነው፤ የድርጅቱ ውድቀት የእኔ
ውድቀት ነው ብሎ የሚያምን አመራርም ያስፈልጋል፡፡ የትም ቦታ አንድ
መሪ ስራውን ቀይሮ ቢወጣ ለሌላ አመራርነት ሊታጭ የሚችለው ከአሁን
ቀደም በመሪነት ደረጃ ያመጣቸው ውጤቶች ታይተው ነው፡፡ የመሪው
ህልውና በቀጥታ ከተቋሙ ህልውና ጋር ይያያዛል፡፡ ዛሬ ላይ ለውጤት
ያበቃ ባህሪ ነገ ሌላ ቦታ ላይ ይኸው ባህሪ አብሮት ይዘልቃል፡፡
ተቃራኒውም እንዲሁ ነው፡፡ በመሆኑም በአመራርነት ደረጃ ላይ
እስከተቀመጠ ድረስ የተቋሙ ውጤት የእኔ ውጤት ውድቀቱም የእኔ
ውድቀት ነው ብሎ ማመን መቻል ይኖርበታል፡፡ ይህ እንደ መሪ
የሚያስፈልግና ለውጤት የሚያበቃ አመለካከት ነው፡፡
#3. S-skill…ችሎታ
“A man who wants to lead the orchestra must turn his
back on the crowd!” Mad Lucado
መሪነት ራሱን የቻለ ችሎታም ነው፡፡ ከሚመሯቸው በላይ የላቀ ችሎታን
ይጠይቃልና አውቶብስ መንዳት ራሱን የቻለ ችሎታ ነው፡፡ ተቋምን
መሾፈርም እንደዚሁ፡፡ የትኛውን ማርሽ በየትኛው ጊዜ ላይ ወስኖ
መጠቀም እንዳለበት መረዳት የሚችል፤ የትኛውን ቁልፍ መንካት
እንዳለበትና እንደሌለበት ማወቅ የሚችል፤ አቅጣጫን የመረዳት ችሎታ፣
የመኪናውን ባህሪ የመረዳትና ማስተካከል የሚችል ችሎታ
ያስፈልገዋል፡፡ አንድ የተቋም አመራርም በተግባር የተፈተሸ ልዩ ልዩ
ችሎታዎች ያስፈልጉታል፡፡ ገንዘብ የማስተዳደር ችሎታ፣ ሰው አስተዳድሮ
የማሰራት ችሎታ፣ ስሜቱን የመቆጣጠር ችሎታ፣ ውጤታማ
ኢንቨስትመንት የማድረግ ችሎታ፣ ተናግሮ የማሳመን ችሎታ፣ የማቀድ
ችሎታ፣ የወደፊቱን የመተንበይ ችሎታ፣ እያለ ይቀጥላል፡፡ አንድ አመራር
ጥሩ ገንቢ አመለካከት ቢኖረው እንኳን ትክክለኛ ችሎታ በሌለበት ሁኔታ
ያለትክክለኛ ትግበራ የሚጠበቀውን ትክክለኛ ውጤት ለማምጣት
ያስቸግረዋል፡፡
#4. K- Knowledge…
“It the blind lead the blind, both shall fall in the
ditch”… Jesus Christ
በእርግጥ ችሎታ የሚዳብረው ከማወቅ ነው፡፡ ለአመራርነት የሚያበቁ
ችሎታዎችን ለማዳበር በቅድሚያ ስለችሎታዎቹ መሰረታዊ እውቀት
ሊኖረው ይገባል፡፡ ሁሉም አይነት እውቀት አይደለም፣ ለትክክለኛ ቦታ
የሚሆን ትክክለኛ እውቀት እንጂ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ ስለሚመራው
ተቋምም ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎችን ሊያውቅ ይገባል፡፡ እንዲሁም
የሚመራው አንድን የንግድ ተቋም ከሆነ ስለንግድ አሰራር መሰረታዊ
እውቀት ያስፈልገዋል፡፡ ብዙውን ጊዜ በአገራችን የድርጅቱ ባለቤት
ስለሆኑ ብቻ እንጂ መሰረታዊ የንግድ ‹‹ሀሁ›› እውቀት ኖሯቸው
ድርጅታቸውን የሚመሩ ሰዎች ጥቂት ናቸው፡፡
አንድ ሰው የሚመራው የእግርኳስ ክለብን ከሆነ ደግሞ ስለ እግርኳስ
መሰረታዊ እውቀትን ሊጨብጥ ይገባል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲም ከሆነም
ስለፖለቲካና አገራዊ አመራር ትክክለኛ እውቀት ያስፈልገዋል፡፡
ምክንያቱም እውቀቱ ችሎታውን ይወስናል፤ ችሎታውን ተግባሩን፡፡
ተግባሩ ደግሞ ባህሪውን ይቀርፃል፡፡ በመጨረሻም የግለሰቡንና
የተቋሙን ውጤት፡፡
ለምሳሌ በአገራችን ያሉ መካከለኛና ከፍተኛ የሚባሉ ኢንተርፕራይዞች
በቀጥታ ለመመራት ያለባቸው በቢዝነስ ሁለተኛ ዲግሪ ባላቸው
ባለሙያዎች ሲሆን ብዙዎቹን ስንመለከት ግን ይህን ሚዛን አያልፉም፡፡
ለዚያም ነው የሚመሯቸው ተቋሞች ወደ ላይና ወደ ታች ሲሉ
የምናያቸው፡፡ በፓርቲም ደረጃ እንዲሁ በፖለቲካል ሳይንስ በቂ ግንዛቤ
ያላቸውን አመራሮች ይጠይቃል፡፡ አለበለዚያ አላዋቂ ሳሚ እንዳይሆን
ራሳችንን መፈተሽ ይገባል፡፡ ለትክክለኛ ተቋምና ለትክክለኛ የአመራር ቦታ
ብቁ የሚያደርግ ትክክለኛ እውቀት!!
#5. E- Experience… ልምድ
“Leadership and (experience) are indispensable to
each other”… John f. Kennedy
ከላይ ያሉት የአመራር ችሎታዎች የሚዳብሩት በልምድ እና በልምምድ
ውስጥ ነው፡፡ እንዲሁም የአመራርነት ባህሪ በራሱ የልምድ ውጤት
ነው፡፡ ከአሁን ቀደም አንድ ሰው ያዳበረው ልምድ ውጤት የማያመጣ
ወይም የውድቀት ከሆነ ባህሪውም ይሄንኑ ነው፡፡ በእርግጥ የአመራር
ችሎታዎቹም ቢሆኑ ውድቀትን የሚያላብሱ ናቸው የሚሆኑት፡፡ በሥራ
ማስታወቂያዎች ላይ ‹‹በዘርፉ ይህን ያህል የሥራ ልምድ›› የሚባለውም
ለዚያ ነው፡፡ የአንድን አመራር ልምድ በቀላሉ ለመረዳት ‹‹ከአሁን ቀደም
ምን ያህል ድርጅቶች አቋቁመህ ወይም መርተህ ለውጤት
አብቅተሃል?›› የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ አንዳንዱ ረጅም ዓመት
የመምራት ልምድ ኖሮት ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ነገር በቦታው ላይ
መቆየቱ አይደለም፡፡ ድርጅቱን ከየት አንስቶ የት አደረሰው? የገጠሙትስ
ተግዳሮቶች ምን ነበሩ? እንዴትስ በመፍታት ተቋሙን ለውጤት አበቃው?
ነው ጨዋታው፡፡ አመራርነት ስልጣን አይደለም ውጤት እንጂ፡፡ ማዕረግ
አይደለም፡፡ አፈፃፀም እንጂ ረጅም ዓመታት በመምራት መቆየትም
አይደለም ረጅም የሚያስከነዳ ውጤትን ማስጨበጡ ላይ ነው ቁም
ነገሩ፡፡
#6. T- Talent… ልዩ ብቃት
“Your are your master, only you have the master key to
pen the inner locks!”
…Leonardo Davienchi
ይህ የአመራርነት የመጨረሻው ማስተሪ ይሉታል ባለሙያዎች፡፡ መሰጠት
እንደማለት ነው፡፡ ታለንት በተፈጥሮ የተሰጠን ሊሆን ይችላል፡፡
በትምህርትና ልምምድም ወደ ማስተርነት የተቀየረም ሊሆን ይችላል፡፡
ከላይ ያሉት ውጤት ተኮር እውቀቶች፣ ውጤት ተኮር ችሎታዎች፣ ውጤት
ተኮር አመለካከቶች፣ ውጤት ተኮር ልምዶች በየጊዜው በዳበሩ ቁጥር
ግለሰቡ ለዚያ ቦታ የሚኖረው ልቀት ያለው አመራር (Leadership
excellence) ወደ ፍፁም ብቃት ይሸጋገራል፡፡ ውጤታማ አመራርነት
ለግለሰቡ ቋንቋው፣ ተግባሩ፣ መንፈሱ፣ መሆን ሲጀምር ሊደርሺፕ በራሱ
ታለንት ወደ መሆን ተሸጋገረ እንለዋለን፡፡
ለዚህ መሰሉ ሰው ውጤታማ አመራርነትን አውቆት ወይም አስቦበት
ሳይሆን ሳያውቀው ሁሉ የሚተገብረው ነው የሚሆነው (autopilot)፡፡
የሊደርሽፕ ማስተሪ ማለት ይህ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአመዛኙ የምናየው
የትምህርት ማስተርስ እንጂ ውጤትና ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ማስተሪ
አይደለም፡፡ ይህ ምናልባት የትምህርት ተቋሞቻችን አንዱ ክፍተት ሊሆን
ይችላል፡፡
ለምሳሌ እኔ ባለፍኩበት የህክምና ሳይንስ ተቋም ማለትም አዲስ አበባ
ዩኒቨርሲቲ እንደ ህክምና ሳይንስ አመለካከታችን በሔታክራተሳዊ
ኤቲክስ፣ እውቀቱ ረጅም ዓመታት የሚፈጅ፣ ከመጀመሪያው ዓመት ጀምሮ
በፍፁም ተግባር ላይ የተንተራሰ፣ ለሶስት ዓመታት ያህል ከሲኒየር
ሐኪሞች ስር በመሆን እንደ ሐኪም ህሙማንን በመመርመርና በማገዝ፣
በተለያዩ ሆስፒታሎች በመዘዋወር ውስጥ ተሞክሮ የተገነባበት በመሆኑ
አንድ የህክምና ዶክተር ከተመረቀ ጀምሮ በየትኛውም ቦታ ላይ
የሚገጥሙትን የስራ ላይ ተግዳሮቶች መወጣት ይችላል፡፡ ድንገተኛ ቀዶ
ህክምና አስፈልጓቸው በገጠሩ በቂ መብራት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ
እንኳን ቀዶጥገና አድርገው ህይወት ያተረፉ፣ እንደዚሁም በቀዶ ህክምና
ያዋለዱ ተመራቂ ጓደኞች ነበሩኝ፡፡ በመሆኑም ሁሉም የትምህርት
ተቋማት ከላይ ያሉትን የአመራር ገጽታዎችን በተሞላ መልኩ የገነቡ
ተተኪ ወጣቶችን ለማፍራት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለይ
የህክምና ሳይንስ ኮሌጆችን ተሞክሮ ቢወስዱ የሚል እምነት አለኝ፡፡
እንዲሁም በዓለማችን ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ ከሆነው
የአሜሪካው ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከሚመረቁ አምስት ሰዎች
ውስጥ አንዱ በአምስት ዓመት ውስጥ ውጤታማ የድርጅት ባለቤት
ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ደግሞ አለማቀፍ ኩባንያዎች ውስጥ
የአንዱ አገር ዲቪዥን የበላይ አመራር ሆኖ የመቀጠር እድል አለው፡፡
ይህ የሚያሳየው ዩኒቨርሲቲው የሚያወጣቸው ተማሪዎች
የ‹‹BASKET›› ፅንሰ ሃሳብን በተላበሰ መልኩ ስለሚያስተምሯቸው
ነው፡፡ በነገራችን ላይ የስመ ገናናው ኢሲኤክክስ መስራች ዶ/ር እሌኒ
ገ/መድህን የዚህ ዩኒቨርሲቲ ውጤት ናት፡፡ ዩኒቨርሲቲ በንግድ ሳይንስ
ካስተማራቸው ውስጥ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ 30 በህይወት ያሉ
ቢሊየነር ነጋዴዎችን ማፍራት የቻለው ከዚህ አንፃር ነው፡፡ እንግዲህ
ቢሊየነሮቹ ይህን ያል ከሆኑ መልቲ ሚሊየነሮቹ ምን ያህል ይሆኑ?
ሚሊየነሮቹስ? እጅግ ብዙ፣ ይህን በእኛ ሀገር ብንፈትሽ ስንቶቹ የንግድ
ሳይንስ ተማሪዎች የት ደርሰዋል? ብለን ማንሳትና ማጥናትም አለብን፡፡
እናም በየትኛውም ተቋማት ውስጥ ለምንቀጥራቸው አመራሮች
እንደመመልመያ መስፈርትም ሆነ መገምገሚያነት እንዲሁም ተተኪ
አመራሮችን ወደ ላይ ለማምጣት የ‹‹B ASKET›› መርህን መከተል
እንችላለን፡፡ በምንመራው ተቋም ውስጥም ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡
እንዲሁም በዚህ መርህ ተተኪ አመራሮችን በኮችንግ፣ በስልጠና
እንዲሁም ከበላይ ካሉ አመራሮች ስር በመሆን እንዲሰሩ በማድረግ
ማብቃት እንችላለን፡፡ በተላዩ የድርጅቱ ክፍሎችና ቅርንጫፎች ውስጥ
በማዟዟር ልዩ ልዩ እውቀትን፣ ልምድንና ችሎታን እንዲያዳብሩ ካደረግን
በኋላ ወደ ላይ ማምጣት እንችላለን፡፡
መንፈሳችን ስለወደዳቸው፣ ደስ ስላለን ወይም ስለመሰለን
የምነቀጥራቸው ወይም ደግሞ የምንተካው ሰዎች መኖር የለበትም፡፡ ደስ
ስላለን ብቻ መኪናችን እንዲነዳልን ቁልፍ ሰጥተን በመኪናው ውስጥ
ተሳፍረን የምንሄድ ስንቶቻችን ነን? አናደርገውም፡፡ ተቋምም እንዲሁ
ነው፡፡

Related posts

Leave a Comment