የአመራር ብቃት – የተፈጥሮ ስጦታ ወይስ ሂደት? (Nature or Nurture?)

የአመራር ብቃት – የተፈጥሮ ስጦታ ወይስ ሂደት? (Nature or Nurture?)

“መሪዎች በሂደት ወደ መሆን ይመጣሉ እንጂ መሪ ሆነው አይወለዱም፡፡ እንደማንኛውም ነገር በብርቱ ስራና ጥረት ወደ መሆን ይመጣሉ” – Vince Lombardi

አንድ ሰው በአመራሩ አስገራሚ የሆነን ስኬት ሲያዝመዘግብ “የአመራር ተሰጥኦ ያለው ሰው ነው” በመባል ይነገርለታል፡፡ ይህ አባባል የአመራር ብቃት ጉዳይ በሂደት የሚዳብር ሳይሆን በተፈጥሮ የሚመጣ እንደሆነ የመጠቆም ባህሪይ አለው፡፡ ከዚህ አመለካከት በመነሳት አንዳንዶች እንደሚያምኑትና እንደሚናገሩት አንድ ሰው ወደ አመራር ለመምጣት በተፈጥሮ መሪ ሆኖ ወይም የአመራርን ብቃት ተክኖ መወለድ አለበት፡፡

በእነዚህ ሰዎች አመለካከት አንድ ሰው ሲወለድ፣ ወይ መሪ ነው ወይም ደግሞ አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡ ይህም አመለካከት ልዩ “የተፈጥሮ ባህሪይ ጽንሰ-ሃሳብ” (Great Man Theory) በመባል ይታወቃል፡፡ በተቃራኒው በሌሎች አመለካከት አመራር የሂደት ጉዳይ ነው – ሰዎች በሂደት የሚማሩት፣ የሚለምዱትና የሚያዳብሩት፡፡

አንዳንድ ሰዎች በተፈጥሮአቸው የመሪነትን ዝንባሌ ይዘው መወለዳቸውን ልንክደው የማንችለው እውነት ነው፡፡ ነገር ግን አነዚህ ሰዎች ያንን ይዘው የተወለዱትን የተፈጥሮ ዝንባሌ ካላሳደጉት በውጤታቸው ከማንም ሰው አይለዩም፡፡ ውጤታማ መሪዎችን ለየት የሚያደርጋቸው ዋነኛ ባህሪይ መማርና መሻሻል ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ሂደትን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡

በመሪነት ዝንባሌ መወለድ – ሁለት አይነት ሰዎች
• በመሪነት ዝንባሌ የተወለደ፣ ዝንባሌውን ግን ያላሳደገ፡፡ ይህ አይነቱ ሰው በውስጡ ይዞ የተወለደውን የመሪነት ዝንባሌ እንዲያሳድግ ይመከራል፡፡
• በመሪነት ዝንባሌ የተወለደ፣ ዝንባሌውንም ያሳደገ፡፡ ይህ አይነቱ ሰው ራሱን በማሻሻሉ እንዲገፋበት ይመከራል፡፡

ከመሪነት ዝንባሌ ውጪ መወለድ – ሁለት አይነት ሰዎች
• ከመሪነት ዝንባሌ ውጪ የተወለደ፣ ዝንባሌውንም ያላሳደገ፡፡ ይህ ሰው ከአመራር ብቃት እጅግ የራቀ ሰው ነው፡፡ ያለችውን “ጠባብ” እድል ግን ተጠቅሞ ራሱን ለመሻሻል መስጠትና ማደግ ይችላል፡፡
• ከመሪነት ዝንባሌ ውጪ የተወለደ፣ ከጊዜ በኋላ ግን የመሪነትን ዝንባሌ ያሳደገ፡፡ ይህ አይነቱ ሰው ራሱን ለማሻሻል ባለው ጥረት ወደ ብቃት በማደግ ላይ ያለ ሰው ነው፡፡

አንድ ሰው ሲወለድ የመሪነትን ዝንባሌ ይዞ መጣም አልመጣ በሂደት ወደ መሪነት ሙላት ሊደርስ እንደሚችል ማሰቡ አሳማኝ ነው፡፡ አመራር ከተፈጥሮ ባህሪይ ጋርና ከሂደት ጋር የመዛመዱን እውነታ ሚዛናዊ ለማድረግ የሚከተሉትን ነጥቦች እለግሳለሁ፡፡

  1. ለጊዜው አመራር አልተሳካልንም ማለት ወደ መሪነት ማደግ አንችልም ማለት አይደለም፡፡
  2. ብንወድም ባንወድም ከመሪነት ራሳችንን ማግለል አንደማንችል እንገንዘብ፡፡
  3. የአመራርን ችሎታ የማይጠይቅ ምንም አይነት ተግባር በምድር ላይ እንደሌለ እናስታውስ፡፡
  4. ወደሚቀጥለው የአመራር ደረጃ ለመድረስ ማድረግ የሚገባንን ነገር እናድርግ፡፡
  5. በፍፁም ከመማር አናቋርጥ፡፡

በነገው ፖሰቴ ተጨማሪ የአመራር እውነታዎችን ይዤ እሰከምመለስ ይህንን በዚህ ጥያቄ ላይ ያላችሁን የግል ግንዛቤ ፖስት በማድረግ አጋሩን፡-

“አንድ ሰው በዛም አነሰም በተፈጥሮ ያገኘውን የአመራር ብቃት ለማሳደግ ምን አይነት መንገዶችን መጠቀም ይችላል?”

Source:- Dr Eyob Mamo

Related posts

Leave a Comment